Thursday, September 15, 2011

የአቶ አንዱዓለም አራጌ፣ የአቶ እስክንድር ነጋና የሌሎች ተከሳሾች የዛሬ የፍርድ ቤት ውሎ- መስከረም 4፤2004 ዓ.ም


“በ2004 ዓ.ም. በሀገሪቱ ውስጥ የሽብር ተግባር ለመፈፀም በቡድን ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ማስረጃ አግኝቼባቸዋለው” በማለት በትናንትናው እለት በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የፓርቲ አመራሮችና ጋዜጠኛ አራዳ የፌደራል መ/ደ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ቀርበዋል፡፡
በቅድምያ በችሎቱ የቀረበው እውቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ነበር፡፡ አጃቢ ፖሊሶች ማንም ሰው ወደ እስረኛው ሆኖ ወደ ችሎቱ እንዳይቀርብ በመከልከላቸው የችሎቱን ሂደት ማንም አልተከታተለውም፡፡ ሆኖም ጋዜጠኞች ዳኛው ጋር በመቅረብ መከልከላችንን አስረድተው ወደ ችሎቱ ለመግባት ለማስፈቀድ ችለዋል፡፡ ቀደም ሲል የቀረበው እስክንድር ነጋ ፖሊሲ የጠየቀውን የ28 ቀን ምርመራ ጊዜ ተጠይቆበት ለጥቅምት 02 /2004 ዓ.ም. በ8፡00 ሰዓት ተቀጥረዋል፡፡
በመቀጠል አቶ ዘመኑ ሞላ የቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ የተከሰሱበትን ጉዳይ ያውቁ እንደሆነ ጠይቆዋቸው፣ ፖሊሲ እንደ ነገረኝ በሽብርተኝነት ተጠርጥረህ ነው ብሎኛ፣ እኔ ስለ ሽብር ተግባር የማውቀው ነገር የለም፡፡ በቅርቡ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር ነኝ፡፡ ፓርቲያችን መስከረም 21 ቀን 2004 ዓ.ም. ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጠይቀን ነበር፡፡ ከዚህ ውጭ የማውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡
ቀጥሎ የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ቤሄራዊ ምክር ቤት አባለት የሆኑት አቶ አሳምነው እና አቶ ናትናሄል መኮንን በቅድመ ተከተላቸው በዳኛው በአቶ ሙሉ ክንፈ ፊት ቀርበው፣ በሽብር ተግባር ተጠርጥረሃል ከመባል ውጭ የፈፀምነው ወንጀል የለም ብለው መልሰዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የ28 ቀን ጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ለጥቅምት 02 /2004 በ8፡00 ሰዓት ቀጥሮዋቸዋል፡፡
በመጨረሻም የቀረበው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ም/ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሁም የመድረክ ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ አንዱዓለም አራጌ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቱ በምን እንደተያዙ ጠይቋዋቸው ፖሊሰ በሽብር ተግባር ነው ብሎኛል ሲሉ መልሰዋል፡፡ ፖሊሲ የ28 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆቦታል፣ የሚሰጡት ሃሳብ አሎት ተብሎ ሲጠየቁ አቶ አንዱዓለም  “አንድ ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ የምናገረው ሃሳብ አለኝ፡፡ እየተፈፀመ ያለው ተግባር የተቃዋሞ ፖለቲካውን ለማፈን የተወሰደ እርምጃ ነው፡፡ ከእንግዲ ወዲያ ፍርድ ቤቱ የፈለገውን እርምጃ ሞትም ቢሆን መውሰድ ይችላል፡፡ ሌላ የምሰጠው አስተያየት የለኝም” ሲሉ መልሰዋል፡፡ በመቀጠልም ዳኛው የምጠይቆት የእርሶን መብት ለማስክበር ነው፡፡ በሚናገሩት ነገር እርምጃ መውሰድ ይችላል፡፡ ፍ/ቤቱ ሊያከብሩ ይገባል ሲሉ ዳኛው አቶ ሙሉ ክንፈ ተናግረዋል፡፡ ፍ/ቤት በነጻ የዳኝነት ስርዓት የሚያከናውን ነው፡፡ በፍርድ ቤቱ አያምኑም? ሲሉ የተናገሩ ሲሆን አቶ አንዱዓለም በመጨረሻም “እኔ ነጻ ነው ብዩ አላስብም” ብለዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል