Sunday, July 31, 2011

አሜሪካ የታየው ስኬታማ ስብሰባ በጀርመንም ተደገመ!

በአብነት በላይ


የግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ተማም ባቲ የተገኙበት ከሦስት ሰዓታት በላይ የወሰደ ታላቅ ስብሰባ ቅዳሜ ጁላይ 30፣ 2011 በጀርመን አገር በኑረምበርግ ከተማ ተካሄደ።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሰብሳቢዎች የተገኙበት ይኸው ስብሰባ በዋነኝነት አብሮ መሥራትን እና አንድነትን በሚጠይቁ ወቅታዊ የፖለቲካ እና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በተለይ በግንቦት ሰባት በኩል በትጋት እየተሰራ ያለውን ከዚህ በፊት በተለያየ ምክንያት ተራርቀው እና በፍራቻ ዓይን ይተያዩ የነበሩ የተለያዩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎችን ወደ ትብብር መድረክ የማምጣት ሥራ የደረሰበትንም ከፍተኛ ደረጃ ያመላከተ ነበር።


ስብሰባው በአቶ ቸኮል ከተከፈተ በኃላ የወቅቱ ጥያቄ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር አስፈላጊነት በሚል መሪ ቃል ንግግራቸውን ያደረጉት አቶ ተማም ባቲ ሲሆኑ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ትግል ዋነኛ ዓላማ ጭቆናን እና ጨቕኞችን ለማስወገድ ነው እንጂ አገርን ለመገነጣጠል አይደለም በማለት ይልቁንም የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ ከፍተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር እንደሚጠይቅና ለሕዝብ ነፃነትና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የሚታገሉ ኃይሎች መበታተን፣ አለመተባበር እና አለመተማመን በሥልጣን ላይ ያለውን የአምባገነኑን የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥት እድሜ ከማራዘም ውጪ አፋኙን የመለስ ሥርዓት ለመጣል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ትልቅ እክል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።

አቶ ባቲ ወያኔ/ኢሕአዴግ በሕዝብ ላይ ያደረሳቸውን እና እያደረሰ ያሉትን ችግሮች በአሁኑም ሰዓት የፈጠረውን የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት አስታውሰው ኦነግ ያለውን ሥርዓት ለማስወገድ ፍትህ፣ ነፃነትና ዲሞክራሲን ዓላማ አርገው ከሚሠሩ ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር በትብብር ለመሥራት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መጨረሱን አስታውቀዋል።

ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔ የሚነዛውን የፍራቻ ፕሮፓጋንዳ በመርሣትና በኦነግ ላይ ያለውን ጥርጣሬ በመተው የጋራ ችግራችንን በጋራ ለማስወገድ «በሕዝቦች እና በድርጅቶች መካከል ትብብር እንዲጎለብት መሥራት የሁላችንም ግዴታ ነው» ሲሉ አቶ ባቲ ጨምረው ገልጸዋል። በድርጅቶች መካከል የሚደረጉ የመቀራረብ ሥራዎች ለመለስ መንግስት ትልቅ ስጋትን እንደሚፈጥርበት ያስገነዘቡት የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባል የትብብሩ ጅማሬ በወያኔ/ኢሕአዴግ ላይ ድንጋጤ ለመፍጠሩ በቅርቡ ኦነግን፣ ኦብነግን እና የግንቦት ሰባት ድርጅቶችን አሸባሪ ድርጅቶች ብሎ መፈረጁን እንደምሳሌ ገልጸዋል። ሕዝብን የማደራጀትና የማንቃት ሥራ፣ ሕዝብን ከወያኔ ጭፍጨፋ ሊታደግ የሚችል የታጠቀ ኃይል እና የዲፕሎማሲ ሥራዋች ያለውን ሥርዓት ለመገርሰስ ኦነግ በዋነኛነት አጽንዖት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሦስት ነጥቦች ናቸው ብሎ ያምናል ብለዋል አቶ ባቲ።በመጨረሻም ከወያኔ ሥርዓት መወገድ በኃላ ኦነግ ሥርዓቱን ለመጣል ከተባበሩ ኃይሎች ጋር እና የኢትዮጽያ ጉዳይ ይመለከተናል ከሚሉ ድርጅቶች ጋር በመሆን የሽግግር መንግስት በማቅቅም የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የሚከበርበት ፍጹም ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሕዝብ የመረጠው መንግስት ሥልጣን የሚይዝበት ሥርዓት ይመሰረታል በማለት ንግግራቸውን አብቅተዋል።


በቀጣይነት ንግግር ያደረጉት የግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሲሆኑ ንግግራቸውን የጀመሩት የእለቱ መነጋገሪያ ርእሳቸው ዋሺንግተን/አርሊንግተን ላይ ያደረጉት መከራከሪያ ሃሳብ የሆነው የኢትዮጵያ አንድነት ቀጣይ ክፍል መሆኑን በማሳሰብ ነበር። የኢትዮጵያ አንድነት ጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም ከባህላችን ከሃይማኖታችን ከቕንቕችን እና ከመሳሰሉት በላይ ፍትህ እና የዜግነት እኩልነት ወሳኝ ነገሮች ናቸው ያሉት ዶ/ር ብርሃኑ በአንዲት ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ባህሎች እና ቋንቋዎች መኖራቸውን ገልጸው ከእነኝህ ይልቅ ለአንድነታችን ዋነኛ ነገር ሊሆን የሚችለው ሁላችንንም የሚያስማማ የፖለቲካ መሰረት ሲኖር ብቻ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከስልሳዎቹ ጀምሮ የብሄር ጥያቄን ያስነሳው ዋነኛ ነገር ባህላችን አልተከበረልንም የሚል ጥያቄ መሆኑን በማውሳት ባህል ለአንድነታችን ምክንያት ሊሆን እንደሚችለው ሁሉ ለመለያየታችን እና አከራካሪ ጥያቄን ለማንሳት መነሻ ሊሆን እንደሚችል በማብራሪያቸው ገልጸዋል። ታሪክም እንዲሁ እንደባህል ሁላችንንም ሊያስማማ እንደማይችል በመጥቀስ መሰረታችን ሊሆን የሚገባው የፍትህ እና የዜግነት እኩልነት መሆኑን አስምረውበታል። የሕግ የበላይነት የሌለበት አገር ውስጥ የባህል የቋንቋ እና ሌሎች አንድ ያደርጉናል የምንላቸው ነገሮች ለልዩነት መምጣት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ብለው የገለጹት ዶ/ር ብርሃኑ የፖለቲካ/የዜግነት እኩልነት ለዚሁ ለአንድነት ሌላኛው ምሰሶ መሆኑን ተናግረዋል። እነኚህ ባልተከበሩበት ኢትዮጵያዊነት ሊኖር እንደማይችልም በመከራከሪያ ሃሳበቸው አንስተዋል። በአጭሩ ኢትዮጵያዊነት እንዲኖር ዴሞክራሲዊነት ቀዳሚው መስፈርት መሆኑን አሳውቀዋል።


ወደ እለቱ ሃሳባቸው ሲገቡ በኢትዮጵያዊነት ላይ የሚነሱት የማንነት ጥያቄዎች ማንነትን በሚያነሱ ኦነግን እና ኦብነግን በመሳሰሉ ኃይሎችም ውስጥ ሊነሱ አይችሉም ወይ በማለት ዶ/ር ብርሃኑ የዋሺንግተኑ/አርሊንግተኑ መከራከርያቸው ቀጣይ የሆነውን ክፍል ከጥያቄያቸው በመነሳት ተንትነዋል። ሲያብራሩም እነኝህ የአንድነት ጥያቄዎች ዘውጎች(ethnic identities) በአንድ ቋንቋ ስለተናገሩ የሚመልሱ አይደሉም ያሉት ዶ/ር ብርሃኑ ማንኛውም ማንነት ዘላቂ የሆነ መደላደል ላይ እንዲያርፍ ከላይ በተጠቀሱት ሁለት መሰረቶች ላይ ማረፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ቋንቋን በተመለከተም ሲናገሩ በዓለም ላይ ያየናቸው ብዙዎቹ ግጭቶች መነሻቸው ቋንቋ አለመሆኑን በመግለጽ በቋንቋ ላይ መሰረት በማድረግ የሚመጣ አንድነት የማንነትን ጥያቄን እንደማይመልስ ግጭትንም እንደማያስቀር አስገንዝበዋል።

ስለዚህም ዛሬ በቋንቋ ላይ ብቻ መሰረት ያደረጉ ማንነቶች ከኢትዮጵያ በመገንጠል መፍትሄ ሊያገኙ አይችሉም ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል። የማንኛችንንም አንድነት የሚያጠናክረው ዋንኛው ነገር በፍትህ እና በፖለቲካ እኩልነት ላይ መሰረት ያደረገ አንድነት መሆኑ ከሚያራርቁን ነገሮች በላይ የሚያቀራርቡን እሴቶች መሆናቸውን በማውሳት በሚያቀራርቡን ነገሮች ላይ ጠንክረን ከሠራን ኢትዮጵያዊነትን ያለ ችግር ማምጣት እንደምንችል ገልጸዋል። የዚህም ሥራ የመጀመርያው መሆን ያለበት የትብብር መድረኮችን ማጠናከር መሆኑን አበክረው ተናግረዋል። ለንግግራቸውም መዝጊያ ሁለት ዋነኛ ያሉትን ነጥቦች አንስተዋል። የመጀመርያው ነጥባቸው ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ በዘውግ የተደራጁ ድርጅቶች በተለይ ኦሮሞዎች የትግሉ መሪ መሆን መቻል አለባቸው ይህንንም ኃላፊነት በመሪነት እስካልተወጡ ድረስ ሁሌም በነሱ ላይ ጥርጣሬ ይኖራል የሚል ሲሆን ሁለተኛው ነጥባቸው ደግሞ ስሜት ለማነሳሳት እና ድጋፍ ለመሰብሰብ ብቻ ሲባሉ የሚደረጉ ጽንፈኝነትን የሚፈጥሩ ኃላፊነት የጎደላቸው ጥሪዎች እና ቅስቀሳዎች መቆም መቻል አለባቸው የሚል ሲሆን በመጨረሻም እድገትና ብልጽግና የዴሞክራሲ፣ የፍትህ እና የእኩልነት መኖርን ግድ እንደሚልና ይህንንም የሚሹ ኢትዮጵያውያን በቀናነት እና በመተባበር እንዲሰሩ የሚያሳስብ መልእክት በማስተላለፍ ንግግራቸውን ዘግተዋል።

ከውይይቱ በኋላ ከተሰብሳቢዎች ለተነሱት በርካታ ጥያቄዎች በአቶ ባቲ እና ዶ/ር ብርሃኑ የተሰጡት ማብራርያ የታከለባቸው መልሶች ለብዙዎች የእስካሁኑን የግንቦት ሰባትን እና የኦነግን የትብብር መድረኮች አመርቂ ውጤት ከማሳየቱም በላይ የወደፊቱን የትግል አቅጣጫ አመላካች ነው። በእለቱ በኑረንበርግ ከተማ እየተካሄደ የነበረውን በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች የእግር ኳስ ፌስቲቫል ለአገራዊ ጉዳይ በማስቀደም የመጡትም በርካታ ኢትዮጵያውያኖች ቁጥር የትብብር መድረኩ በብዙኃኑ የተሰጠውን ጠንካራ አመለካከት አሳይትዋል።