Friday, August 5, 2011

«እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ» 1 ነገ.22፥17


በኤርምያስ ኅሩይ


 ከብረት በጸና እምነቱና በቅንነቱ ኅሩይ፣ ልበ አምላክ፣ ፍቁር ተብሎ በእግዚአብሔርም በሰውም አንደበት እንደተሞገሰ እንደ ዳዊት ወይም እንደ ጥበበኛው ልጁ እንደ ሰሎሞን በበጎ ሥራ ባይሆንም በነጋሢነቱና መገሥጸ ነገሥት ከሆነው ከነቢዩ ኤልያስ ጋር ባለው ተያያዥ ታሪክ ስሙ የሚታወቀው ንጉሠ እስራኤል አክዓብ በሕይወት ዘመኑ የመጨረሻ ቀናት ሶርያን በጦር ወግቶ ሬማት ዘገለዓድን የእስራኤል አካል የማድረግ እቅድ ነበረው። እቅዱም በይሁዳው ንጉሥ በኢዩሳፍጥና በቧለሟሎቹ ዘንድ ድጋፍ የተቸረው በብዙ የሳቱ ነቢያቱም የተሞካሸ እቅድ ነበር። ከነቢዩ ከሚክያስ በቀር የሰልፉ ውጤት ሞት እንጂ ድል እንደማይሆን ያለመም የተነበየም አልነበረም። የሰው ሰልፍ ፍጻሜውም ኅሣር እንጂ ክብር፤ ኪሣራ እንጂ ትርፍ እንዳልሆነ ከፈጣሪው ዘንድ ተገልጦለት ስለተረዳ ንጉሡ «ለሰልፍ ልሂድ?» ብሎ ላቀረበለት ጥያቄ «ወጥተህ ተከናወን!» በማለት የሚጠብቀውን ውድቀት ሲገልጽለት በአስረጅነት የነበረው የራእዩ መሪ ቃል «እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ» የሚል ነበር።
     አክዓብ ንጉሥ ነበር። ጠላት መውጋት ድንበር ማስፋት ደግሞ የንጉሥ ሥራ ነበር፤ ታዲያ ለምን ሰልፉ ተነቀፈበት? ለምንስ ረድኤተ እግዚአብሔር ተለየው? ለምንስ ውድቀት ታዘዘበት? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ ይሆናል ልንጠይቅም ይገባል። እስኪ ወደኃላ መለስ ብለን የቀደመ ታሪኩን በጥቂቱ እናስታውስ። አክዓብ በሚስቱ በኤልዛቤል ምክርና አሳብ የሚመራ፤ ካህናትንና ነቢያትን በመግደልና በማሳደድ እንዲሁም በመቶዎች የተቆጠሩ ጣዖታትን በማቆም የሚስቱ ተባባሪና የክፋት ፊትአውራሪ ነበር። ኃላም የእስራኤላዊ ናቡቴን ብቸኛ ርስት በግፍ በመንጠቅና እርሱንም በማስገደል እግዚአብሔር ለነቢዩ ኤልያስ ያዳኘበት በገዘፉ ስህተቶችና በደሎች የተከሰሰ በደለኛ ሰው ነበር። እንዲህ ያለ ሰው ታዲያ የሚሰለፈው ሰልፍ ሁሉ ራሱን ለማድለብ ካልሆነ በቀር እግዚአብሔርን ለማገልገል እስራኤልን ለመጥቀም ነው ተብሎ እንደምን ይገመታል? እግዚአብሔር በመንጋው ላይ ሾሞታልና ከልቡ ግሣት ይልቅ የእግዚአብሔርን ድምፅ ሊሰማና ሁሉ የእርሱ ለሆነም የእስራኤል አምላክ ቁራጭ መሬት ለመማረክ ከመጣደፍ በፊት ራሱን ለፈጣሪው ማስማረክ መንፈሱንም ለአምላኩ ግዳይ መጣል ይገባው ነበር። እርሱ ግን ይህን አላደረገም። እግዚአብሔር በአንደበቱ የተናገረበትን ነቢዩንም ሊሰማው አልፈለገም እንደውም እንደጠላት ግዞት አወረደው። እርሱም ተሰለፈ ቀስት ወረወረ ውጤቱ ግን እንደተገልፀው ድል ሳይሆን ሽንፈት፤ ክብር ሳይሆን ውርደት ሆነ። እርሱም በቀስት ወደቀ እስራኤልም አውራ እንደሌለው ንብ ከጠላቶቻቸው ፊት ሸሽተው ተበተኑ።
     ይህን ታሪክ ያነሣሁት ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚነገረው ዜና ወይም ለእኔ ብቻ የተገለጠልኝ ከሌሎች የተሠወረ ኖሮኝ ሳይሆን ከጊዜ ወደጊዜ በዓይነትና በመጠን እየበዛ በመጣው ፈርጀ ብዙ ውስጣዊና አፍአዊ ችግር ሳቢያ ቅድስትና ሐዋርያዊት ቤተክርስትያናችን የተጋረጡባት አደገኛ ፈተናዎች ያሳደሩብኝን በቤተክርስቲያኒቱ አናት ላይ የሚንፎለፎለውን የፈተና ፏፏቴ እያዩ ሀገር ሰላም ብሎ መተኛቱ በክርስቶስ ዘንድ ማስጠየቁ ስለማይቀር በዚህ ትውልድ ጊዜ ገጥሞን በሕይወት ያለን ምእመናን በጸሎትም በምክርም ከኃጢአት ዓለም በጸጋ የታደገችንን እናት ቤ/ክ የጠላት ጦር ባይጥላትም እንዳያቆስላት ባይፈታትም እንዳያላላት በዚህ ጊዜ ታዳጊውን አምላክ ይዘን ልንቆምላት እንደሚገባ ከማሳሰብ ዝም እንዳልል ኅሊናዬ ስለሞገተኝ ነው።
በርግጥ / የሰላም መልእክተኛ ብትሆንም 2ሺህ ዘመናት ታሪኳ ሰላምን በማይሹ አጋንንትና ሠራዊቶቻቸው ስትፈተን ስትገፋ የኖረች፤ ስለ ዓለሙ ሰላም የሐዋርያቶቿንና የምእመናን ልጆቿን ደም የገበርች ነገር ግን ጠላቶቿ ሲወድቁ ሳትወድቅ በብዙ ጭንቅ ውስጥ አልፋ ዛሬም እንደ ትናንቱ ስለ ዓለሙ ሰላምና ደኅንነት በመዓልትና በሌሊት በነግህና በሠርክ እየጸለየች አማናዊ መሥዋዕት እየሠዋች ትገኛለች። ጌታ በወንጌል «የሲኦል ደጃፎች አይበረቱባትም» ማቴ. 1618 ብሏልና ጠላት እንደምንም ቢበረታ መቼም መች በረድኤተ እግዚአብሔር ተጠብቃ የምትኖር መሆኗን አምናለሁ። ነገር ግን እረኞች ጳጳሳትና ካህናት፤ መንጋዎች ምእመናን ከተሠራልን ሥርዓት ወጥተን ሥጋዊ ሰልፍ ስንሰለፍ ብንገኝ አንደኛችን መውደቃችን ሌላኛችን መበተናችን እንደማይቀር «የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ» የተባለች የኢየሩሳሌም ተደጋጋሚ ውድቅትና ትንሣኤ ያስተምረናል። በመግቢያዬ ያነሣሁት የአክዓብ ውድቅት ታሪክም የሚያስረዳው ይህንኑ ነው።
ከዚህ አንፃር / በተለይ ካለፉት 2 ዓመታት ወዲህ የሰሚን ጆሮ እስኪያሰለች ድረስ ስም አጠራሯ በከበረች ጥንታዊትና ኦርቶዶክሳዊት / ላይ ሊናገሩት የሚከብድ የገንዘብ ብክነት፣ ሹመትን፣ አምባገነንነትን፣ ወገንተኛነትንና የመሳሰሉትን አሳፋሪ ተግባራት መሠረት ያደረጉ ክሶችና ግብግቦች ተካሂደውባታል። ችግሩን ከሥሩ ለማጥራት ጥረት አለመደረጉን ቢደረግም ስኬታማ አለመሆኑን አሁንም በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል ያለው ውጥረት፤ ከሀገር ውጪም በተለያዩ ሀገሮች ባሉ አብያተ ክርስትያናትና ምእመናን መካከል የሀገር ቤት ሲኖዶስ፣ የአሜሪካ ሲኖዶስ ተባብሎ መከፋፈሉ ያስከተለው ጉዳት አስረጂዎች ናቸው። መፍትሔ ሳያገኝ ለወራት የዘለቀው የአዋሳ /ስብከት ችግርና ሌሎችም በየቦታው እየፈነዱ ያሉ ጥቃቅን ችግሮች የተጠቀሰው ዐቢይ ችግር ውጤቶችና በቤ/ክኒቱ ላይ የተጋረጠውን ፈተና ሊያቀጣጥሉ የሚችሉ ጋዝና ቤንዚን እንዳይሆኑ የሚያሰጉ ክስተቶች ናቸው።
አሁን ዓለም ካጤናቸው የቤ/ክኒቱ ችግር መንሥኤዎች አንዱ የገንዘብ ብክነት ነው። በዚህ አጀንዳ እንደኔ አሳሳቢው ጥያቄ ማን? እንዴት? ስንት? የሚለው ሳይሆን ለምን ዓላማና አገልግሎት የሚውል ገንዘብ? የሚለው ነው። አላግባብ ያጠፉ ያጎደሉ አይጠየቁ ለማለት አይደለም ይጠየቁ ይቀጡ እንዲያውም ቅዱስ ዳዊት «በላዩ ኃጢአተኛን ሹም ሰይጣንም በቀኙ ይቁም በሚከራከርም ጊዜ ተረትቶ ይውጣ» መዝ. 108፥6 እንዳለ ቤ/ክኒቱን ለቀው ቦታቸውን ይያዙ እላለሁ። ለበጎ አብነት ተጠርተው የክፉ ሥራ አብነት ከሆኑ ቤ/ክንን ምን ሊበጇት?
          ለምን ዓላማ የሚውል ገንዘብ? ተብሎ ቅድሚያ ሊጠየቅ ይገባል ያልሁት የቤ/ክ ተልዕኮ ምእመናንን ማስተማር፣ ማጥመቅ፣ ማቁረብ፤ ብሎም አረጋውያንን መጦር፣ የሙት ልጆችን ማሳደግ፣ ስደተኞችንና ሕሙማንን መርዳት መንከባከብ ወ.ዘ.ተ ነው። ታዲያ ባከነ የሚባለው ገንዘብ ይህን ለመሰለ አገልግሎት የተመደበ ገንዘብ ነበር ወይስ ለሌላ ሥጋዊና ቁሳዊ ተግባር? እኔ እስከሚገባኝ በካህንና በንዋያተ ቅድሳት እጦት የተዘጉ አብያተክርስትያናትን ለመክፈት ወንጌል በበቂ ሁኔታ ባልተሰበከባቸው መሥዋዕት ባልተሠዋባቸው በስም ብቻ ክርስቲያን ነን እያሉ የሚኖሩ ምእመናንን በአገልግሎት ለመድረስ ወይም በሌላ ምግባረ ሠናይ ጉዳይ የተመደበም የባከነም ገንዘብ የለም። ብክነቱ የሚፈጸመው ከዚህ ውጪ በሆነ ጉዳይ መሆኑ ግን እጅግ ያሳዝናል።
          በእርግጥ የባከነ ገንዘብ በፍርድ ሊመለስ ይችላል ጠብና ንትርክ በመጥላት ከቤ/ክ የሸሹና እየሸሹ ይሉትን ምሁራንና በቤታቸው የተወሰኑትን ምእመናን እንዲሁም አጋጣሚውን ተጠቅመው የወተወቱአቸውን መናፍቃን ተከትለው የባዘኑትን የእግዚአብሔር በጎች እንዴት አድርጎ ነው ወደ ቤታቸው መመለስ የሚቻለው? ችግር ለምን ተከሰተ ማለት አይቻልም ቤ/ክ የጽድቅ መድረክ ናትና ፈተና ሊኖር ግድ ነው። ጥያቄው ለምን መፍትሔ አይፈለግለትም? ለምን ችግር በችግርነቱ ወራትን ዓመታትን እንዲያስቆጥር ይፈቀድለታል? መፍትሔስ ተገኝቶላቸው ውሳኔ የተላለፈባቸው ጉዳዮች ለምን ተፈጻሚ ሲሆኑ አናይም። እስካሁን ፍትሕ ፈልገው ያለመታከት በሀቅ የሚጮኹትን የአዋሳ ምእመናን እጅግ አደንቃለሁ ገንዘባቸውን ጊዜያቸውን ሠውተው ለቤ/ክ ሲሉ አዲስ አበባ ድረስ በመመላለስ አቤት ማለታቸው በክርስቶስ ዘንድ ታላቅ ክብር የሚያሰጥ ተጋድሎ ነው። ጋዜጣ ተጻፈ፤ በሚድያ ተለፈፈ ግን ምን አተረፈ? በርግጥ ከችግሮች በስተጀርባ ያሉ አትራፊዎች አላተረፉም ማለት አይቻልም። ቤ/ክ ግን በዚህ ሰልፍ ተጠቃሚ አለመሆኗን አምናለሁ። ጌታ በወንጌል ለእረኞች የሰጠው መመሪያ «ያለ ዋጋ የተቀበላችሁትን ያለ ዋጋ ስጡ በመቀነታችሁም ወርቅ ወይም ብር ወይም መሐልቅ አትያዙ» ማቴ. 10፥9 የሚል ነበር። እኮ እንደ ሐዋርያት ያለ ዋጋ ማገልገል ቀርቶ በተመደበ ደመወዝ ተወስኖ መኖርም አቅቶን የዚህ ዘመን እረኞች ከዓመት እስከ ዓመት በገንዘብና በቁሳቁስ ስንተማማ ስንካሰስ መኖራችን፤ በአንዲት ቤ/ክ ውስጥ ሁለት ሲኖዶስ በአንዲት ቤ/ክ ውስጥ አምስት እና ስድስት ቡድኖች አበጅተን እርስ በእርስ መፋለማችን ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ የሚበቃ ቁጥር ያላቸው ጳጳሳት አንዲት የኢትዮጵያን ቤ/ክ አረጋግቶ መምራት እንዴት አቃታቸው? ለ3ሺህ ዓመታት አንድ ሆነው መቅደሳቸውንም ሀገራቸውንም ያስከበሩ ምእመናን ታመሱ ተብሎ ዕለት ዕለት ሲለፈፍ መስማታችን ይህ አያሳፍርም? በእውነት በሚጠሉንና ውድቀታችንን ከሚሹ አሳዳጆቻችን ፊት በኅፍረት እንድንሸሽ እያደረገን ነው።
          ውኃ ድንጋይ ካልጣሉበት አይጮህም። መንፈሳዊ ጸጥታ ሰፍኖባት የኖረች ቤ/ክ አሁን ዘመን ላይ የሁከት መድረክ እየሆነች መምጣቷ ሰይጣን ባጎነው ደንጊያ መሆኑን ከደንጊያው ጋር ደግሞ ፓለቲካ፣ ቢዝነስ፣ ኑፋቄንና ዘረኝነትን የመሳሰሉ ጠጠሮች አብረው መኖራቸው ግልጽ ነው። ለዚህም ነው ችግር ተከስቶ ቶሎ የማይከስመው። በዚህ ውዥንብር ምን ያህል የእግዚአብሔር በጎች በተኩላ ተነጥቀዋል? ከጥቂቶች በስተቀር ማን ግድ ሰጥቶት ቆጠረው? የበጎቹ ባለቤት እግዚአብሔር ግን በእያንዳንዲቱ በግ መጥፋት ያዝናል። ቤ/ክ ስለጠፉ ልጆቿ ታለቅሳለች። አባቶች እባካችሁ ሰልፋችሁን አስተካክሉ! ጊዜው ሊውጡን የተነሡትን አሳዳጃችንን በፍጹም መንፈሳዊነት የምንቋቋምበት እየጠፉ ያሉ በጎችን የምንታደግበት እንጂ ለሹመት የምንሯሯጥበት ገንዘብ እየተመናተፍን የምንካሰስበት ጊዜ አይደለም። እኛ ጎራ ለይተን ስንሰለፍ በጎናችን ቆመው እንደተቆርቋሪ ሆይ ሆይ የሚሉንን ሰዎች ማንነትና ዓላማ በቅጡ እናጢነው። ሁሉም ሰልፈኞች አለመሆናቸው እንደ አክዓብ ለግል ምርኳቸው ራሳቸውን ያሰለፉ መኖራቸውን አንዘንጋ። በዚህ ትርምስ በጎች መጥፋታቸውን ብቻ አይደለም ተኩላዎች በግ መስለው መግባታቸውን በማስመሰል መሾም መሸለማቸውንና በእረኞች ወንበርም መቀመጥ እየቻሉ መሆናቸውን እናስተውል። የውስጥ ጉዳያችንን መፍታት ሳንችል እየቀረን የፖለቲካ ዓላማ ላላቸው ሰዎች ቅድስት ቤ/ክንን አጋልጠን አንስጥ። ቤ/ክ የአምልኮ እንጂ የፖለቲካ ጉዳይ ማስፈጸሚያ ቦታ አይደለችም። የቤታችንን ጉዳይ አቅም በፈቀደ አባቶቻችን ከነሱ በላይ ለሆነው ደግሞ ወደ ፈጣሪ ማንጋጠጥ እንጂ ወደ ፖለቲከኞች መመልከቱ ችግሩን ቢያብስ እንጂ አያሽለውም። ምእመናንም ቅር ባሰኘን ነገር አቤት ማለታችን ተገቢ ሆኖ ለበጎ የጮህነው ለከፋ እንዳይሆን ቅዱስ ጳውሎስ «ፀሐይ ሳይጠልቅ ቁጣችሁን አብርዱ» ብሎ እንደመከረን ጠባችንን ሳናውል ሳናሳድር ለማስወገድ እንጣር። ስለ ቤ/ክ ክብር እየተውን እየተሸነፍን ቤ/ክንን እንጠብቃት አንድነት እንጂ ሁለትነት ኅብረት እንጂ ቡድንነት ፈጽሞ የሚጠቅመን አይደለም። ስለዚህም አኩርፈን የሸሸንም፣ ቤ/ክኒቱን ለካህናት ብቻ ትተን ቸል ያልናትም ሁሉ አብረን መክረን አብረን በጸሎት ተግተን ቤ/ክኒቱን ወደ ቀደመ ይዞታዋ ልንመልሳት ለሚጠላትና ለሚያሳድዷትም ሁሉ ወለል አድርገን የከፈትነውን በር ፈጥነን ልንዘጋው ይገባል እላለሁ። ሰልፋችን ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን።
ሰላመ እግዚአብሔር አይለየን