Wednesday, October 5, 2011

አሥራ ስድስት የደርግ ባለሥልጣናት ተፈቱ


በጌቱ ጥበበ- በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰው በሞትና በዕድሜ ልክ እስር እንዲቀጡ ከተወሰነባቸው የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል 16ቱ ተፈቱ፡፡
በዘር ማጥፋት ወንጀል ከተከሰሱት 23 ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል 20 ዓመት በእስር ያሳለፉት 16 ባለሥልጣናት በአመክሮ በትናንትናው ዕለት ተፈትተዋል፡፡

ትናንትና የተፈቱት ባለሥልጣናት የቀድሞው የደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ፣ ሻምበል ለገሰ አስፋው፣ ኮሎኔል እንዳለ ተሰማ፣ ሜጀር ጀነራል ውብሸት ደሴ፣ ሌተና ኮሎኔል ናደው ዘካሪያስ፣ መቶ አለቃ ጴጥሮስ ገብሬ፣ መቶ አለቃ ስለሺ መንገሻ፣ ሻለቃ ደጀኔ ወንድማገኘሁ፣ አቶ እሸቱ ሸንቁጤ፣ አቶ ልሳኑ ሞላ፣ ብርጋዴር ጄነራል ለገሰ በላይነህ፣ አቶ ገስግስ ገብረ መስቀል፣ አቶ አበበ እሸቱ፣ አቶ በሪሁን ማሞና መቶ አለቃ ደሳለኝ በላይ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹም ባለሥልጣናት 20 ዓመት ሲሞላቸው ጊዜያቸውን ጠብቀው ይለቀቃሉ ተብሏል፡፡

ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር በወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነየሱስ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንና በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሃይማኖት መሪዎች፣ በደርግ ዘመን የተፈጸመው በደልና ጥፋት፣ በአገራዊ ይቅርታና እርቅ እንዲጨረስና ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የእርቁና የይቅርታው ተካፋይ እንዲሆን ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡ በወቅቱ ባለሥልጣናቱ የፈጸሙዋቸውን የተለያዩ ወንጀሎች በማመን እግዚአብሔርን፣ ሕዝብንና መንግሥትን ይቅርታ መጠየቅ እንደፈለጉ የሃይማኖት መሪዎቹ አስታውቀው ነበር፡፡ የእርቅና የሰላም ሥራ የአገሪቱ የተሀድሶ አንዱ አካል በመሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት እንዲያውቁት መደረጉን የገለጹት የሃይማኖት መሪዎቹ፣ በዘመኑ የተፈጸመው በደል ፈጣሪንም፣ ሰውንም ያሳዘነ እንደነበር በመግለጽ ምሕረትንና ይቅርታን መጠየቅ እንደሚገባ አሳስበው ነበር፡፡

ከአራቱም የሃይማኖት ተቋማት የተውጣጣ ዓብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለሁለት ዓመታት መሥራቱን የገለጹት የሃይማኖት መሪዎቹ፣ በዘመኑ ጥፋት ሰለባ ከነበሩ ማኅበራት ጋር በመመካከር መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸው ነበር፡፡ ሆኖም የሃይማኖት መሪዎቹ የይቅርታና የእርቅ ጥያቄ ከተለያዩ አካላት ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ በተለይም በደርግ ሥርዓት ተጐጂ ከነበሩና ከተጐጂ ቤተሰቦች የሃይማኖት መሪዎቹ የጀመሩት የይሁንታና የይቅርታ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የባሥልጣናቱ ከእስር የመፈታት ጉዳይ ዘጠኝ ወራትን ካሳለፈ በኋላ፣ 16ቱ ባለሥልጣናት ትናንትና ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወጥተዋል፡፡ ከባለሥልጣናቱ መካከል በደርግ ዘመን የደኅንነት ሚኒስትር የነበሩት ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል፡፡