በጌቱ ጥበበ- በዕለት ተዕለት ግላዊና ማኅበራዊ ሕይወት የሚያጋጥም ማንኛውንም አጋጣሚ፣ አሳብንና ውሳጣዊ ስሜትን ደስታንና ኀዘንን ማግኘትና ማጣትን ተስፈኛነትንና ተስፋ ቢስነትን ለሁለተኛና ለሦስተኛ ወገን መግለጥ ማንጸባረቅ ማጋራት ሰውን ከሌሎች ሥጋዊና ደማዊ ፍጥረቶች ልዩ ከሚያደርጉት ሰብአዊ ባሕርዮቹ መካከል አንዱና ምናልባትም የራሱ የሆነ ሥርዓትና መለያ ጠባያት ላሉት የሰው ልጅ ኑሮ ከመብልና ከመጠጥ ቀጥሎ አስፈላጊና ወሳኝ ከሆኑት ሰብአዊ ፍላጎቶች ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዝ የመሠረታዊ ፍላጎቶች ሁሉ ማግኛ ማጣፈጫ ማዋሀጃና ማስፈጸሚያ መሣሪያ ነው። ሰው በተፈጥሮ የተሰጠውን ልዩ የማሰብ ችሎታ ተጠቅሞ መጥፎም ይሁን ጥሩ በየጊዜው ለዓለማችን እንግዳ የሆኑ ነገሮችን አምጥቷል፤ የአኗኗር ስልቱንና ይዘቱንም በየጊዜው በማሻሻል ተፈጥሮን በሚገባ መጠቀምና የጥንት ሰዎች ይኖሩት ከነበረው አኗኗር እጅግ የተሻለና የተደራጀ ቀላልና ምቹ ኑሮ ለመኖር ችሏል። ማሰብ እስካልተቋረጠ ድረስ በሰው ልጆች አኗኗር የሚታየው መሻሻልና መደላደል አይቋረጥም ፧ በእያንዳንዱ አዲስ ቀን ዓለም የሰው ልጅ አሳብና ዕውቀት ውጤቶች የሆኑ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን እንደ ገጸ በረከት ስትቀበል ትኖራለች።
ማሰብ ለሰው ልጆች ኑሮ መለወጥ ማደግና መበልጸግ ያበረከተውን አቻ የሌለው አስተዋጽኦ፣ ማሰብ አለመቻል ደግሞ ለእንስሳት ኑሮ አለመለወጥ የተጫወተውን ሚና እንመልከት፧ሰው ሰው ነበረ አሁንም ሰው ነው ማሰቡ ግን “የሚያስብ እንስሳ” የሚለውን ስያሜ ውሸት አድርጎ ምናልባትም “ልዩና ድንቅ ፍጥረት” ሊባል የሚችልበት የኑሮ እድገት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ረድቶታል፤ እንስሳት ግን አሁንም እንስሳት ብቻ ናቸው ኑሯቸውም ያው የጥንቱ መተኛት መነሣት መብላት መጠጣት ትናንትም ዛሬም አቀርቅሮ ሳር መንጨት! ይሁን እንጂ ማሰብ ብቻውን የሰውን ሁለንተናዊ ሁኔታ ለመለወጥና ለማሻሻል በቂ አይደለም አሳብን መግለጥ ማካፈል መቻል ሌላው አስፈላጊው ነገር ነው እንደውም አሳቡን መግለጥ ባይችል ኖሮ ሰው ከአንድ ጊዜ በላይ ሊያስብ አይችልም ነበር፤ ካልተናገረው ምን ሊፈይድለት በማሰብ ይደክማል? ልክ እንደ እንስሳት መብላት መጠጣት ሆድ ሲሞላ መቦረቅ ሲጎድል መኮራመት በቃ ሕይወቱ ኑሮው እንዲህ ባለ ትርጉም አልባ ሂደት ሊወሰንና ለዛ ቃና ጣዕም የለሽ ሊሆን ግድ ይሆን ነበር። አሳቡን መግለጥ በመቻሉ ግን ማሰብን መደበኛ ሥራው አድርጎ ሁሌ ያስባል ያቅዳል ይመራመራል እንግዲህ ቀላልና ምቹ ኖሮ ለመኖር ያገዙት የቴክኖሎጂ ውጤቶች የማሰብ ብቻ ሳይሆኑ አሳብን መግለጥ የመቻል ፍሬዎች ናቸው። እንደ ማሰብ ሁሉ አሳብን መግለጥም በተፈጥሮ የተገኘ ሀብትና ሰው ሁሉ ከሌላ ወገን ፈቃድና ስምምነት ሳያስፈልገው በራሱ ፍላጎትና ተነሣሽነት ሊከውነው የሚችለው የተፈጥሮ መብት ነው፥ በርግጥ አሳብ ሁሉ ጠቃሚና ትክክል ነው ሊባል አይችልም ትክክል ያልሆነንም አሳብ ማስተጋባት ምናልባት ከአሳቢው አልፎ በሌሎች ወገኖች አስተሳሰብና እምነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አያሳድርም ማለት አያስደፍርም፥ አሳብን በአሳብ ማረም ማስተካከል የበተከውን አስተሳሰብ በነጠረ አመለካከት ማቃናት ሲቻል ለምን አሰብክ ለምን ተናገርክ ማለት ግን የሰውን ተፈጥሮአዊ መብት የሚገፍ ጸያፍ ተግባር ነው። ይህን የመሰለ አመለካከት ጎልቶ የሚታየው ራሳቸውን በፈጣሪ ቦታ አስቀምጠው ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር እንደ እንስሳት እነርሱ በፈለጉት ሁኔታ ብቻ ለመንዳት ከሚፈልጉ ፈርዖናዊ አንጎል በተሸከሙ አልያም የተሻለ ማሰብና አሳብን በአሳብ የማሸነፍ አቅም ችሎታና ትዕግሥት እንደሌላቸው አምነው ክብራቸውን ዝናቸውንና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ማሰብንና አሳብን መግለጽን መዋጋት እንደሆነ በሚያምኑ ደካሞች ሰዎች ነው። የእነዚህን ሰዎች ውጥንቅጥና ውል አልባ ጠባይ መተረክ አይከብድም ፍላጎታቸውን በትክክል መረዳትና እንዲህ ነው ብሎ መናገር ግን ያስቸግራል፥ አሳብንና አሳቢን ለሥልጣኔ ለጥቅሜ አደገኛ ነው ብለው ሲያሳድዱ ሲታዩ ራስወዳድ ሊመስሉ ይችላሉ በርግጥ ራሳቸውንስ ቢሆን ይወዳሉ? ተብሎ ሲጠየቅ ግን ርሳቸውን መውደዳቸውም አጠራጣሪ ነው ምክንያቱም በቀን ሦስት አራት ጊዜ ሲበሉ ቢያንስ አንድ ጊዜ እንኳ ቢያስቡ አሳብን እንደ ገጸ በረከት በደስታ ተቀብለው ተፈትሾ ተሞክሮ ጠቃሚ ሆኖ ቢገኝ በውጤቱ ለመጠቀም ይጓጉ ነበር እንጂ እንደ ተስቦ ፈርተው ወደ ውስጣቸው እንዳይዘልቅ የልባቸውን በር አይዘጉም አሳቢዎችንም እንደገጸ በረከት አቅራቢ ፍቅርና አክብሮትን ይቸሯቸው ነበር እንጂ እንደ መርዘኛ ጠላት አያሳድዷቸውም ነበር።
የጥንቱ ጠበብቶች መርከብና ድልድይ እንሥራ ሲሉ መሪዎቻቸው ለመንግሥታችን አደገኛ ነው ብለው ከልክለዋቸው ቢሆን ኖሮ የቅርብ ጊዜዎቹም ሳይንቲስቶች አይሮፕላንና ባቡር እናምርት ሲሉ አስተዳዳሪዎቻቸው ተንኮለኞች ናችሁ ብለው ቀጥተዋቸው ቢሆን እነርሱም እኛም እንደ ጥንቱ በበቅሎና በፈረስ ጀርባ ተንጠልጥለን እንቀር ነበር እንጂ ምቾቱ በተጠበቀ የአየር የባሕርና የየብስ መጓጓዣ መንፈላለስ አንችልም ነበር፤ እንግዲህ ኑሮን ጣር ያልበዛበት ቀላልና ምቹ ለማድረግ እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ያስገኙ ጠበብቶች ማሰብና አሳብን መግለጽ ሳይፈቀድላቸው ቀርቶ ፎርሙላቸውን በጭንቅላታቸው እንደያዙ ቢሞቱ ኖሮ ይህን የመሰለ ጠቃሚና አስፈላጊ ነገር ሳናገኝ እንቀር እንደነበር አስተውሉ። ይህን እንደምሳሌ ጠቀስኩኝ እንጂ በማንኛውም ዘርፍ የሚደረግ የአሳብ መንሸራሸር ለሀገርና ለማኅበረሰባዊ እመርታ አሌ የማይባል ጠቀሜታ አለው። ታዲያ ለራሳቸውም ሆነ ለሌላው ሰብአዊ ፍጡር የተሻለ ነገር ለማምጣት የሚጠቅሙ አዳዲስ አሳቦችን የሚጻረሩ መሪዎች ሀገራቸውንና ወገኖቻቸውን አይደለም ራሳቸውን ይወዳሉ ማለት አስቸጋሪ ነው፤ የማይጠረቃ ሆዳቸውን ለመሙላት የዕለት ዳቧቸውን ከማብሰል በቀር ለነጋቸው እንኳ የማያስቡ የተሻለ ነገር የተሻለ ጊዜ ለውጥ የማይናፍቃቸው በማመንና በማሳመን ከሚገኝ አንጻራዊ ሰላም ይልቅ በኃይልና በአፈና የሚሸቀጥ ጊዜያዊ ጸጥታ የሚያረካቸው ልበ ደንዳኖች ናቸው። መቼም ስለማንና ስለምን እንደምናገር ለአንባቢ የሚሠወር አይመስለኝም አዎን ከኢትዮጵያውያን አልፎ ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ አሳሳቢ የሆነው በሀገራችን የመጻፍና የመናገር መብት ድፍን ብሎ መጥፋትና ለሀገርና ለወገን ይበጃሉ የሚሏቸውን አሳቦች የሚያፈልቁና ለሕዝብ የሚያካፍሉ ዜጎች እየታደኑ መታሠርና በእሥር ቤት መማቀቅ- ስለዚህ ጉዳይ ነው።
ምሁራን ጋዜጠኞች የሲቪል ማኅበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት ወዘተ በመንግሥት አስተዳደርና ፖሊሲ ላይ ያላቸውን ቅሬታ የሚገልጹ ከሙስናና ከዘረኝነት የጸዳና የይስሙላ ዲሞክራሲ ሳይሆን ሊተገበር የሚችል እውነተኛ ዲሞክራሲ የሰፈነበት የሰከነ አስተዳደር ለማምጣት በትምህርትና ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ የቀሰሙትን በጎ አሳብ የሚለግሡ ዜጎች ሁሉ አሸባሪ የሚል ስም እየተለጠፈባቸው በእስርና እንግልት መሠቃየታቸው ያልተያዙትም ለስደት መዳረጋቸው ተባብሶ መቀጠሉን ዓለም ካወቀው ሰነባብቷል ተጽፏል ተተንትኗል እስካሁን ግን በመንግሥት በኩል የተለሳለሰ ሁኔታ አልታየም የዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎችን ሪፖርት ተመልክቶ ለምን እንዴት ብሎ በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ አንድ ርምጃ የተራመደ ዓለማቀፋዊ ኅብረት ወይም መንግሥትም የለም፤ ነገሩን አተኩረው ሲያዩት መንግሥት የተነፈሰውን ሁሉ እንዲያስር እንዲያሠቃይ ዜጎች ደግሞ እንደ እንስሳት የራሳችን አሳብ ሳይኖረን ለሥልጣናቸው የጊዜ ገደብ በሌላቸው መሪዎች አሳብ ብቻ እየተነዳን እንድንኖር የተፈረደብን ይመስላል፤ ኧረ ለመሆኑ ማሰብ አሳብን መግለጽ ወንጀል መሆኑ አብቅቶ ስለሀገራችን ስለኑሮአችን በነጻነት የማሰብ የማቀድና የመወያየት ተፈጥሮአዊና የዜግነት መብታችን የሚከበረው መቼ ይሆን? እንስሳት ተፈጥሮ ዝም ባታሰኛቸው አጎንብሰው ባይቀሩና ቀና ብለው አካባቢያቸውን በአግባቡ ማስተዋል ቢችሉ ኖሮ ለምን ሣር ብቻ በመጋጥ እንወሰናለን ብለው ማሰብ በጀመሩ አሳባቸውንም ተገላልጸው ሌላው ቢቀር ተጨማሪ ምግብ ለራሳቸው ባገኙ ምናልባትም ከሣርና ከድርቆሽ የተሻለ! እኛም አቀርቅረን ዝም እንድንል ተገደን ባንኖር ማሰብ በቻልን አስበን አስበን አሳባችንም በነጻነት ተገላልጸን የሰላምና የምጣኔ ሀብት እድገት እንቅፋቶች የሆኑትን ነገሮችና ሁሉ ከላያችን አራግፈን የሀገራችንን ዕድገት ተጽፎ የሚነበብ ብቻ ሳይሆን በዓይን የሚታይ ማድረግ ኑሯችንን በራሳችን ዕውቀት አቅምና የተፈጥሮ ሀብት የሚታይና የሚዳሰስ አማናዊ ማድረግ በቻልን ነበር።
አሳብ ሲታፈን አሳቢዎች ሲኰነኑ እድገትና ልማት አብረው እንደታፈኑ በቀላሉ ሊገኝ ይችል የነበረ የተሻለ ኑሮና ስኬት እንደተጨናገፈ ማስተዋል ያስፈልጋል። በርግጥ ኢትዮጵያችን ብታድግ ብትለማ ሰላምና መረጋጋት ቢሰፍንባት ዜጎች ተከባብረውና ተፈቃቅረው ያለልዩነት በእኩልነት ቢኖሩባት መሪዎች የሚያጡት ነገር ይኖር ይሆን? ለእኔ እንደ ዜግነቴ የሚታየኝ የግለሰቦቹ ብቻ ሳይሆኑ የመላው ኅብረተሰብና የሀገሪቱ እድገትና የሰላሟ ተቀናቃኞች ሆነው ነው! እና እስከመቼ በፀረ ኢትዮጵያ አስተሳሰብና አቋም የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ድምጽና እስትንፋስ ታፍኖ ይኖራል እስከመቼ መናገር ወንጀል ሆኖ ያስገርፋል? እንደዚህ ዓይነቱ ቅጥ ያጣ አፈና በቃ ሊባል ይገባዋል ዕድገታችንና ልማታችን ከአሳቢ ዜጎቻችን ጋር መታሠራቸው ሊቆም ይገባል ይህን የሕዝብ የልብ ትርታ ሁሉም ሊያስተጋባውና ዓለማቀፉም ኅብረተሰብ ድምጻችንን ሰምቶ ለሰብአዊ መብታችን መከበርና በእስር ለሚሠቃዩ ት ወገኖቻችን መፈታት ከሕዝቡ ጐን እንዲቆሙ ሰብአዊ መብትን ለሚጥስ መንግሥት ምንም ዓይነት ድጋፍ መስጠት እየተጐዳ ላለው ምስኪን ሕዝብ መሠቃየት ተባባሪ መሆን እንደሆነ ዐውቀው ድጋፍ መስጠታቸውን አቁመው በቃህ እንዲሉት ድምጽን ማሰማት ያስፈልጋል።ድምጻችንን ስሙን ዝምታችንንም አዳምጡ አፍ ባይናገርም ልብም እኮ ይናገራል ዝምታም እኮ ይመሰክራል ስሙን አዳምጡን እንበላቸው። ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!