በጌቱ ጥበበ
ይህ ሆኖ ሳለ በነኝህ ባለፉት ዓመታትም ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ድርጅቶች ዋነኛ ትኩረታቸው አድርገው ይሠሩ የነበረው አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ በማስወገድ ላይ የነበረ መሆኑ ግልጽ ነው። በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ተቀራርቦ ለመሥራት ንግግር የነበረ ቢሆንም ውጤታማ ሆኖ አላየነውም። ይህ ሊሆን የቻለበት ዋነኛው ምክንያት የድርጅቶቹ የመነጋገርያ ርዕሰ ጉዳይ ወያኔን እንዴት እንጣለው እንጂ ከዛ በኃላ የሚኖረው ሥርዓት ምን መምሰል አለበት በሚለው ላይ አለማተኮሩ ነው።
ምንም እንኳን ያንድነት ትግሉ ወያኔን ለማስወገድ ትልቅ ቦታ ቢኖረውም ትግሉን በጽኑ መሠረት ላይ ለመጣልና በዋነኝነት ለትግሉ ስኬታማነት እንቅፋት የሆነውን የመፈራራት እና ያለመተማመንን ጉዳይ ለማስውገድ ከወያኔ ውድቀት ወድያ ስለምትገነባው የዜግነት እኩልነት፤ የሰብአዊ፣ የፖለቲካዊና የኤኮኖሚ መብቶች የሚጠበቁባት፣ ሁሉንም ግለሰብም ሆነ ቡድን በእኩል የሚያስተናግድ የፍትህ ሥርዓት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ንግግር፣ ምክክር፣ ውይይት ምርጫ የሌለው ጎዳና ነው። ይህ ዓይነቱ የበሰለ አካሄድ ከለውጥ በኃላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የርስ-በርስ ግጭቶችን ከማስቀረት አኳያ ትልቅ ቦታ ይኖረዋል። ለዚህም ሲባል ነው ይህ ሰሞኑን እያየነው ያለው የውይይት መድረክ ዓይነቶች ጠንክረው መሠራት አለባቸው፣ ተበራክተው ተግባራዊ ሊሆኑ በሚችሉ አሳቦች ዳብረው እንያቸው የምንለው። በዚህ ጉዳይ ካሁኑ ጠንክረን ከሠራን አምባገነኑ የመለስ ሥርዓት ከተወገደ በኃላ ያለስጋት ነገሮችን ልናስኬድ፣ ፍትህ እና የዜግነት እኩልነት ያለባት አዲሲቷን ኢትዮጵያን በቀላሉ ልንገነባ እንችላለን። ድር ቢያብር አንበሳ ያስር አይደል የሚባለው ከነተረቱ። አዎ እናብር!
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል- በተለይም ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉቱ- እያየነው ያለው የትብብር መድረክ የወያኔ/ኢሕአዴግን አገዛዝ ለመጣል በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ከዚህ ቀደም ብዙም ያልተሠራበት ይህ ዓይነቱ የትብብር መድረክ ለውጥን ለማምጣት ካለው አዎንታዊ አስትዋጽዖ ባሻገር ከለውጥ በኃላ መመሥረት አለበት ለምንለው ሥርዓት ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው አከራካሪ አይደለም።
የወያኔ አገዛዝ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡን ዘርን በተለይም ቋንቋን መሠረት በማድረግ ለመከፋፈል እና በአንድነት ሊመጡበት የሚችሉትን ተቃውሞዎች ለማዳከም የተከተለው መንገድ የሥልጣን እርፉን እንደያዘ እንዲቀጥልና ሊደርስብኝ ይችላል ብሎ ካሰበው ተቃውሞ በተወሰነም ደረጃ ቢሆን ሊታደገው ችሏል። ይህንንም ለማድረግ ያስችለው ዘንድ በሌሎች ሀገራት ላይ ተሞክሮ በአንድ ሀገር ሕዝብ መካከል ግጭትን ለማስወገድ ይሄነው የሚባል ውጤት ያላሳየውን ይልቁንም ለርስ-በርስ ግጭት ምክንያት የሆነውን በዘር/ቋንቋ ላይ መሠረተ ያደረገ የፌዴራል ሥርዓት በመዘርጋትና የኢትዮጵያን ታሪክ አንድነትን ሊያዳክም፣ በሕዝብ መካከል ጥላቻን እና ጠብን ሊፈጥር በሚችል መልኩ እንደገና በመጻፍና በመተረክ የከፋፍለህ ግዛ ዓላማውን ለማሳካት ሞክሮዋል። ላለፉት 20 ዓመታትም ሙሉ በሙሉም ባይሆን በተወሰነ ደረጃ የዚህ ዓላማውን ግብ ሊያሳካ ችሏል። በሕዝብም መካከል መፈራራትን እና ርስ-በርስ መከባበርንና አመኔታ ማጣትን ፈጥሯል። ይህም ያንድነትን ትግል ማዳከሙ የማይካድ ያደባባይ ሐቅ ነው።